በግንዛቤ ላይ ተመስርተው በሠላም ይድረሱ!

ማስታወቂያ

የተገደበ እይታ - ምሳሌዎች


በየቀኑ በሚተላለፉ የትራፊክ አደጋ ዘገባዎች ላይ ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል የሚለውን ምክንያት በተደጋጋሚ እናደምጣለን። ለነዚህ አደጋዎች አንዱና ዋነኛው መንስኤ አሽከርካሪዎች እይታቸው የተገደበ በሚሆንበት ወቅት ለዚህ እውቅና ሰጥተው ለሁኔታው በሚመጥን መልኩ ፍጥነት አለመቀንስ ነው። በግልባጩ እግረኞች ለአሽከርካሪዎች ላይታዩ እንደሚችሉ ባለማወቅ፣ በሌሎች ተሽከርካሪዎች ተሸፍነው፣ በጭለማ ተጋርደው፤ መንገድ ላይ መንቀሳቀሳቸው ነው።

ከዚህ በታች የተቀመጡት ምሳሌዎች የተገደበ እይታ የሚፈጠርባቸውን ሁኔታዎች ለመጠቆም እና ግንዛቤ ለማስያዝ ነው።

ወደ ግራ የሚዞሩት ተሽከርካሪዎች ዕይታዬን በእጅጉ ስለሚገድቡት፣ ፍጥነት ቀንሼ በትኩረት አሽከረክራለሁ፡፡

ነጩ መኪና ወደ ግራ እየዞረ ሲሆን እኔ ደግሞ የቀኙን ረድፍ በመያዝ ላልፈው እየሞከርኩ ነው። እይታዬ በነጩ መኪና የተገደበ በመሆኑ ድንገት እግረኛ፤ ተሽከርካሪ ብቅ ሊል ስለሚችል ፍጥነት ቀንሼ፣ ሙሉ ትኩረት ሰጥቼ አልፋለሁ።

አውቶቡሱ ደርቦ ቆሟል። እይታዬ እጅግ የተገደበ በመሆኑ፣ እግረኛ/ብስክሌተኛ ወዘተ ድንገት ጥልቅ ቢሉ በበቂ ርቀት አስቀድሜ ላያቸው አልችልም። በመሆኑም ፍጥነቴን ቀንሼ፣ ሙሉ ትኩረቴን ሰጥቼ በዝግታ አልፋለሁ።

አይሱዙ ወደ ቀኝ ለመዞር የቀኙን ፍሬቻ እያበራ ነው። የግራውን ረድፍ ይዤ ለማለፍ ስሞክር፣ የተገደበ እይታ ስላለኝ፣ ፍጥነት ቀንሼ፣ ሙሉ ትኩረት በማድረግ እጓዛለሁ።

ከፊቴ የሚገኘው የጭነት ተሽከርካሪ ለመዞር የግራ ፍሬቻ እያበራ ይገኛል። ከእሱ ፊት የሚያቋርጥ እግረኛ፣ የሚዞር ተሽከርካሪ ቢኖር አስቀድሜ ማየት ስለማልችል ፍጥነቴን ቀንሼ፣ ከሙሉ ትኩረት ጋር በዝግታ አልፋለሁ።

በቂ የመንገድ መብራት በሌለበት ሁኔታ፣ ይዞታው የተስተካከለ መኪና እያሽከረከርን እንኳን፣ እይታችን በእጅጉ የተገደበ ነው። ለምሳሌ በቀኝ በኩል ከላይ ቀይ ልብስ ያደረገ እግረኛ አለ(ቀዩን ቀስት ይመልከቱ)። ግን በቀላሉ አይታይም። አደጋን መከላከል በበቂ ርቀት አስቀድሞ ማየትን ይጠይቃል። በመሆኑም በእንዲህ ያለ ሁኔታ ፍጥነትን ወደ 30-40 ኪሜ/ሰዓት ገድቦ በትኩረት ማሽከርከር ይገባል።


የመንገድ መብራቶች ጠፍተው ሙሉ ጭለማ ነው። በተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጡ ተሽከርካሪዎች መብራት ያንጸባርቃል። በዚህ መሃል ከግራ ወደ ቀኝ የሚያቋርጥ እግረኛ አለ(ቀዩን ቀስት ይመልከቱ)። የኔ መኪና የፊት መብራት የተሟላ ቢሆንም ይህ እግረኛ በደንብ አይታየኝም። በመሆኑም በእንዲህ ያለ ሁኔታ ፍጥነቴን ቀንሼ በፍጹም ትኩረት አሽከረክራለሁ።


በቀዳሚው ምስል ላይ የሚሻገረው እግረኛ አሁንም አለ(ቀዩን ቀስት ይመልከቱ)። ነገር ግን አሁንም በደንብ አይታየኝም። እግረኞች ይህን መገንዘብ አለባቸው። አሽከርካሪዎች ላያይዋቸው እንደሚችሉ አውቀው የራሳቸውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።


እዚህም የመንገድ መብራቶች ጠፍተዋል፤ እይታዬ የተገደበ ነው። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው መንገዱን እያቋረጠ ያለ እግረኛ ቢንኖርም እያየሁት አይደለም። በእንዲህ ያለ ሁኔታ አሽከርካሪዎች ፍጥነት መቀነስ፣ አለመዘናጋት፤ እግረኞች ደግሞ አሽከርካሪው ይጠንቀቅልኝ በሚል መንፈስ መንቀሳቀስ የለባቸውም።


በቀዳሚው ምስል ላይ ላየው ያልቻልኩት እግረኛ አሁን ከ1 ሰከንድ በኋላ እይታዬ ውስጥ ገብቷል(ቀዩን ቀስት ይመልከቱ)። ይሁን እንጂ ፍጥነት ካለ ይህን እግረኛ የመግጨት እድሌ ከፍ ያለ ነው። ምንጊዜም የተገደበ እይታ ባለበት ሁኔታ ፍጥነት እንቀንስ፤ ሳንዘናጋ በትኩረት እናሽከርክር።


« 1 2 »