በግንዛቤ ላይ ተመስርተው በሠላም ይድረሱ!

ማስታወቂያ

ከፊታችን ከሚገኘው ተሽከርካሪ ጋር መጠበቅ የሚገባን ርቀት - መከተያ ርቀት

ከፊታችን ከሚገኘው ተሽከርካሪ ጋር መጠበቅ የሚገባን ርቀት አንድ ወጥ እና ቋሚ ሳይሆን ከፍጥነታችን አንፃር ተለዋዋጭ ነው። ፍጥነታችን ከፍ ባለ ቁጥር ይህም ርቀት በተመጣጣኝ ሁኔታ አብሮ ከፍ ማለት ይገባዋል።

ይህንንም ለመፈጸም ፣ በጥሩ የአየር እና የዕይታ ሁኔታ፣ ከፊታችን ከሚገኘው ተሽከርካሪ ጋር በ2 ሰከንድ የምንጓዘውን ርቀት፤ በዝናባማ እና በአስቸጋሪ የዕይታ ሁኔታ ደግሞ በ4 ሰከንድ የምንጓዘውን ርቀት መጠበቅ አለብን።

 

ይህን እንዴት መፈፀም ይቻላል?

ይህንን በቀላሉ ለመፈፀም የፊታችን ተሽከርካሪ አንድ ቋሚ የሆነ ምልክትን ሲያልፍ ጠብቀን “One Thousand One, One Thousand Two” እያልን እኛ እዚያ ምልክት ላይ ለመድረስ የሚያስፈልጉንን ሰከንዶች እንቆጥራለን። ከ2 ሰከንድ በፊት ምልክቱ ላይ ከደረስን የመከተያ ርቀታችን ከፍጥነታችን አኳያ በቂ አይደለም፤ ከፊታችን ካለው መኪና ጋር ያለን ርቀት የ2 ሰከንድ እስኪሆን ከፍ ልናደርገው ይገባል ማለት ነው።

ከላይ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ እንደሚታየው፣ የፊተኛው ተሽከርካሪ መንገዱ ላይ የተቀቡትን ነጭ አግድም መስመሮች እንዳለፈ “One Thousand One, One Thousand Two” እያልኩ በመቁጠር እኔ እነዚያ መስመሮች ላይ ለመድረስ የ2 ሰከንድ ርቀት ይፈጅብኛል። ይህ ለደህንነት ተገቢ የመከተያ ርቀት ነው።

በአስቸጋሪ የአየርና የዕይታ ሁኔታ ቢሆን ደግማ የመከተያ ርቀታችንን ከ2 ሰከንድ ወደ 4 ሰከንድ ከፍ ማድረግ ይገባናል ማለት ነው።

 

ይህን በማወቃችን ምን ድምዳሜ ላይ እንደርሳለን?

በሌሎች ገፆች ላይ በዝርዝር እንደምንመለከተው የምንገኝበትን ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ በቂ ርቀት መጠበቅና ፍጥነታችንን መገደብ እንደሚገባን እንገነዘባለን።